ታህሣሥ 19/2013
በሀገራችን ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በፊት በፌደራሊዝም ስም በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ፍፁም አምባ ገነናዊ ስርዓት ተወግዶ ተስፋ ሰጭ ለውጥ በመምጣቱ የሀገራችን ህዝቦች ከነበረው አፋኝ ስርኣት እፎይታን አግንተዋል፡፡
ለውጡ ህዝባችን በፈለገው መጠንና በተፈለገው አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ባይሄድም በኢኮኖሚ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች አበረታች የሆኑ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡ የመጣባቸውና የሀገራችንን እድገት እና ልማት የማይመኙ በቅርብም በሩቅም ያሉ ሀይሎች የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ ከለውጡ ማግስት ጀመሮ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አንዲሁም አብሮነትና አንድነት እዳይኖር እንቅልፍ አጥተው ሌት ተቀን በመስራት ሀገራችን ተረጋግታ ለውጡ ግቡን እንዳይመታ እዛም እዚህም ግጭት በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ እነዚህ የጁንታው ርዝራዦች ብዙ እየታተሩ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ግዜ ሃገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመጀመር
በኢኮኖሚ ወደ ፊት ለመገስገስ ጥረትና ርብርብን እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት የድህረ-ጁንታ ተስፈኞች ከሀገራችን ህዝብ ፍላጎት በተፃረረ መልኩ በቅርብ ካሉ የውጭ ሀይሎች ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ግጭቶችን በመፍጠር ዜጎች እንዲሞቱ፤ እንዲፈናቀሉ እና እንዲሰደዱ በማድረግ በሀገራችን ሰላም እንዳይኖር ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ እኩይ ተግባርም የለውጥ ካባ የደረቡና ከክልል እስከ ፈደራል መንግስት ከፍተኛ መዋቅር ላይ የተቀመጡ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ባለስልጣናት ከለውጡ በተፃራሪ ከቆሙ ፀረ ለውጥና ሰላም ሀይሎች ባልተናነሰ ሁኔታ ህዝብን ወደ ትርምስ ለማስገባት ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ለአብነትም ሠሞኑን በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ክልላዊ መንግስት አዋሳኝ አካባቢ በተጠነሰሰው የግጭት ሤራ የብዙ ንጹሃን ህይወት አልፏል። ይህ ግጭት ሳይበርድ ደግሞ ታህሣሥ 18/2013 በገዋኒ ወረዳ ዉስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች (ፊሪትሊና ሪፎ) ላይ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና ኢትዮጵያን የሚያዋስኑ አጎራባች ከሆኑ የሱማሌ ሀገራት ጭምር የተሳተፉበት እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ሰራዊት ከላይ በተጠቀሱ ቀበሌዎች ላይ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በአፋር አርብቶ አደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በአፋር ክልል ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ በገዳማይቱ ኡነዳፎኦ እና አዳይቱ መንደሮች ላይ የሰፈሩት የኢሳ ሱማሌዎች ከሱማሌ ክልላዊ መንግስት እና አጎራባች የሱማሌ መንግስታት በሚደረግ ሙሉ ወታደራዊ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የአፋር አከባቢዎች በከፈቱት መጠነ ሰፊ ጦርነት ምንም እራሳቸውን መከላከል በማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በሆኑ ህፃናት፣ እናቶች እና አዛውንቶች በእንቅልፍ ላይ ሳሉ በተከፈተባቸው ድንገተኛ ጥቃት መጨፍቸፋቸው የሚታወስ ነው፡፡ ለአብነትም ያህል በኦብኖ እና በአዋሽ ጎርፍ ሙላት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በገላአሉ ወረዳ ደቡዳሌ ቀበሌ ላይ ሰፍረው በነበሩ አርብቶ አደሮች በዲሽቃ እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ጭፍጨፋ መካሄዱን በቦታው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት የሚያውቀው ጉዳይ ሲሆን መከላከያም እነዚህን አሸባሪዎች ጦርነቱን እንዲያቆሙ የኢትዮጵያን ባንዲራ በመያዝ ቢሞክሩም የተባበሩትን የሱማሌ ጦር በመከላከያም ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ ጅራፍ እራሱ ገርፎ አረራሱ ይጮሀል እንደሚባለው አሸባሪዎቹ የሱማሊ ወራሪዎች የሱማሌ ክልላዊ መንግስትን ጨምሮ እንደዚሁም የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰብ ይወክላሉ ተብለው የተቀመጡት የፌደሬሽን አፈጉባኤው አቶ አደም ፋራህ ባወጡት መግለጫ ወረራው የአፋር ልዩ ሃይል ገዳማይቱ ላይ ጭፍጨፋ እንዳካሄደ የተለመደ ቅጥፈታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እያላዘኑ ይገኛሉ፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጣውን ጀግናውን መከላከያ ሰራዊታችን ከአፋር ጋር አብሮ እንደጨፈጨፋቸውና ዘረፋም እንዳካሄደባቸው የስም ማጥፋት ዘመቻም ከፍቶባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት በገዋኔ ወረዳ ላይ በድሽቃና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች በመታገዝ ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ጥቃት በአከባቢው ላይ በነበሩ አርብቶ አደሮች እና እንስሳት ላይ ውድመት ከመድረሱም ባሻገር በአየሉ ተራራ ላይ ለአንድ ቀን ሙሉ በቆየው የዲሽቃ ድብደባ ምክንያት በተራራው ላይ የነበሩ ሳርና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ወድመዋል፡፡ በመሰረቱ ይህ ዲሽቃ የተባለው መሳሪያ እና ሌሎች ወራሪዎቹ የሱማሌ ሃይሎች የሚጠቀሙበት ከባድ መሳሪያዎች መገኘት ያለባቸው በአገሪቷ የመከላከያ ሰራዊት እጅ ብቻ መሆኑ ቢታወቅም ወራሪዎቹ እነዚህን መሳሪያዎች መታጠቃቸው ከሀገራችን ህግ ጋር የሚጣረስ መሆኑ ግልፅ ሲሆን ስለ ወረራው እጅግ የተሳሳተ መግለጫ እያወጡ የሚገኙት የሱማሌ ክልላዊ መንግስት እና የፌደሬሽን አፈጉባኤው ስለነዚህ መሳሪያዎች በህግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ በመጨረሻም ከዚህ በታች ለተገለፁት አካላት የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) የሚከተለውን መለዕክት ያስተላልፋል፡፡
1ኛ. ለብዙሃን መገናኛዎች
በአፋር ህዝብ ላይ በተባበሩት የሱማሌ ሀይሎች እየተካሄደ ያለውን ወረራ በማስመልከት እየተሰሩ ያሉ ዜናዎች እና ዘገባዎች በመገናኛ ብዙሃን ከመለቀቃቸው በፊት ጦርነቱ የት እና በማን እንደሚካሄድ እንዲሁም ለምን ዓላማ እንደሚካሄድ የተሟላ መረጃ ሳይገኝ መተላለፋቸው ተገቢ አለመሆናቸውን እየገለፅን ሁሉም ይህን የተሳሳተ መረጃና ዘገባ ሲሰሩ እና ሲያሰራጩ የነበሩ የብዙሃን መገናኛዎች ወደ አከባቢው መጥተው የተሟላ መረጃ አግኝተው ጉዳዩን ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቁ እንጠይቃለን፡፡ የአካቢቢዉን ስሞችም በትክክል በእትዮጵያ የካርታ ድርጅት አሰያየም እንዲጠሩ እናሳስባለን። የግዛት ማስፋፋት ዓላማን ለመሳካት ተብሎና አካባቢው የኢሳ በማስመሰል (ጋድማይቱን-ጋርባኢሤ) ወዘተ እየተባለ የሚዘገበው እንዲቆም እናሳስባለን።
2ኛ. ለሱማሌ ክልል መንግስት
የሱማሌ ክልል አመራሮችም ሆኑ አብዛኛው የኢሣ ማህበረሰብ የአፋር ህዝብ በቀዬው እየተወረረና እየተገደለ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተጓዳኝ በኢኮኖሚውና በፖለትካው ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ጥቂት ቡድኖች ደግሞ የግዛት ማስፋፋት እንዲሁም የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ሃዲድ መስመር እንደተቆጣጠርነው ሁሉ በአፋር የሚያልፈዉን የኢትዮ-ጂቡቲን መንገድ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አለብን የሚሉ ህልመኞች ህዝብ ከህዝብ በማጣላት ሥራ ተጠምደው እንዳሉ እናዉቃለን። ለሶማሌ ክልል ወንድሞቻችን የምናሳስበው እነዚህን ህልመኞችን ተቆጣጠሩና ይልቁን ለቀጠናው ሰላምና ለህዝባችን እድገት አብረን እንስራ እንላለን። በተጨማሪም የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ጉዳዩን ከማባባስ ይልቅ ሰላም እንዲሰፍን ወደ አፋር ክልል ያስገባቸውን የራሱንም ሆነ ሌሎች ፀረ ሰላም ሃይሎችን ከአፋር ክልል እንዲያስወጣና ጉዳዩን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ በአንክሮ እናሳስባለን፡፡
3ኛ. የአፋር ክልላዊ መንግስት
የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነት እንዳለበት ተረድቶ ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር ከሁለት ዓመት በላይ በክልሉ ላይ እየተካሄደ ያለውን ወረራ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ በአጭር ግዜ ውስጥ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ጠንክሮ እንዲሰራ እና በወራሪዎቹ ጉዳት የደረሰባቸውን የክልሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን መልሶ እንዲያቋቁም እናሳስባለን፡፡
4ኛ. ለኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር
በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በመደገፍ እና በመቀበል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ በመወሰን ሰላማዊ ትግሉን መቀላቀላችሁ ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ ሲሆን በአፋር ክልል ላይ እየተደረገ ያለውን ወረራ መኮነን ሲገባችሁ በተቃራኒው ግን ድርጅታችሁ ባወጣው መግለጫ በአፋር አርብቶ አደሮች ላይ የሚደረገውን ወረራ አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ ገልፃችኋል፡፡ ይሁን እንጂ መግለጫችሁ የሚያመለክተው ነገር ቢኖር ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ የገባችሁትን ቃል የሚያፈርስ ከመሆኑም በላይ መግለጫችሁ በወረራው ላይ ያላችሁን ተሳትፎ በግልፅ ያስቀመጠ ነው፡፡ ይህም ድርጊት ከአንድ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ከሚል የፖለቲካ ድርጅት የማይጠበቅ መሆኑን እየገለፅን ከድርጊታችሁ የማትቆጠቡ ከሆነ ግን እዛም ቤት እሳት አለ የሚለውን ብሂል እንድትገነዘቡት በአንክሮ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
5ኛ. ለኢፌድሪ መንግስት
የሶማሊዎች የቆየ የድንበር ማስፋፋት አባዜ አሁን ካለው የለውጥ መንግስት በፊትም ከ50 ዓመት በላይ የቆየ አጀንዳ ሲሆን በተለያዩ ወቅት የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት ለጉዳዩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ሳይሰጡ ችግሩ ጎላ ብሎ ሲከሰት ብቻ ጊዚያዊ መፍትሄ እየሰጡ እስከ አሁን ድረስ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ የተቋረጠው የሁለቱ ክልሎች ወሰን የማካለል ስራ በአስቸኳይ እንዲካለል በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
6ኛ. ለኢፌድ ሪ መከላከያ ሰራዊት
ከዚህ ቀደም በገዳማይቱ ከተማ ላይ ሰላም ለማስከበር በአካሄዳችሁት እንቅስቃሴ ምክንያት በውስጥም ሆነ በውጭም በሚገኙ የሱማሌ ተወላጆች በተከፈተባችሁ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተገቢነት የሌለው ፍፁም ከእውነት የራቀ በመሆኑ የጀመራችሁት የሰላም ማስከበር ስራችሁን ከምን ግዜውም በበለጠ አጠናክራችሁ በመቀጠል የአፋርም ሆነ ሌሎች በኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ ላይ የሚካሄደውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ህገ መንግስታዊ ተልዕኮአችሁን እንድትወጡ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ይጠይቃል፡፡
ለሰላም ሁላችንም ትግተን እንስራ!!
የአፋር ህዝብ ፓርቲ